Sunday, October 20, 2013

 
Ephrem Eshete
ብዙ ጊዜ ለልጆቻቸው ስም ማውጣት የሚፈልጉ ወላጆች፣ የልጆቻቸው ስም አፍ ላይ ሲጠሩት ደስ ደስ የሚል፣ ቢቻል ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ካልሆነም፣ ከአገራችንም ቢሆን እንዲያው ያልተለመደ ቢሆን ደስ ይላቸዋል። ከእነርሱ አንዱ “ሶልያና” የሚል ለሴቶች የሚወጣ ስም ነው። በቅርቡ አንዲት የፌስቡክ ወዳጄ “ትርጉሙ ምንድነው? የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልና ምዕራፍ ላይ ይገኛል?” ስትል አፋጠጠችኝ። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደሌለ ከነገርኳት በኋላ ትርጉሙን ግን ከየት አባቴ ላምጣው።

ብዙ ሰው ጠየቅዅ። ድጓው “ጊዜ ዕረፍታ ለሶልያና” ብሎ በጥር ስለ እመቤታችን ዕረፍት ከሚናገረው በቀር ትርጉሙን ማግኘት አልቻልኩም ነበር። የማታ ማታ፣ መጽሐፍ ተገኝታ፣ ትርጓሜውን አበራችልኝ። ለካስ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ተርጉመውት ኖሯል። ስንት ቦታ ሳስስ የሳቸውን መዝገበ ቃላት ማየት ስችል። “ሶልያና፤ (ጽር፣ ሴሊኒ)፤ ጨረቃ፤ ድንግል ማርያም፤ ‘ጊዜ ዕረፍታ ለሶልያና’፤ (ድጓ)።” በአጭር ቃል ሶልያና ማለት ጨረቃ እንደ ማለት ነው። የእመቤታችንም መጠሪያ ነው። ቅዱስ ያሬድ ክርስቶስ ፀሐየ ጽድቅ ስለሆነ እናቱ ደግሞ “ጨረቃ ናት” ለማለት ተጠቅሞበት እንደሆን እንጃ። የድጓውን ሊቃውንት መጠየቅ ነው።